Skip to main content

                 

Image removed. የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ እና አጠቃላይ ገፅታImage removed.

                                           
 
  የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ 

በ2015 ዓመተ ምህረት በተካሄደው ህዝብ ውሳኔ ውጤት መሰረት የቀድሞው የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አካል የነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛው የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ሆኖ አንዲደራጅ በኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ ፤ በቀድሞው የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲተደደሩ የነበሩት ቀሪዎቹ የጉራጌ፣ የሀዲያ፣ የስልጤ፣ የካምባታና ጠምባሮ፣ የሀላባ ዞኖች እና የየም ልዩ ወረዳ ሪፎርም በማድረግ በጋራ በአንድ ክልል አንዲደራጁ በተወሰነው መሰረት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ነሀሴ 13 ቀን 2015 ዓመተ ምሀረት ተመሰረተ፡፡ 

የማዕክላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ዓ.ም. አንቀጽ 47 መሠረት ከተመሰረቱት ክልሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ክልሉ የሚገኘዉ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ አቅጣጫ ሲሆን ብዝሃ ማዕከላት እንዲኖሩት ተደርጎ የተዋቀረ ሲሆን የመስተዳድር ምክር ቤት መቀመጫው ሆሳዕና ከተማ ነው፡፡

                   የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ አጠቃላይ ገፅታ

 የክልሉ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ከ7 004’ እስከ 8 003’ ሰሜናዊ ኬክሮስ እና ከ37020’ እስከ 38060’ ምሥራቃዊ ኬንትሮሰ ላይ ነው፡፡ አዋሳኞቹም በሰሜን፣ በምእራብና በምስራቅ አቅጣጫ ከኦሮሚያ ክልል፤ በደቡብ በኩል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በደቡብ ምዕራብ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ይዋሰናል፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅሩም በዞኖች፣" በልዩ ወረዳዎች፣" በወረዳዎች፣" በከተማ አስተዳደሮችና በቀበሌዎች የተደራጀ ነው:: ክልሉ 1,515,.600 ሄ/ር ስፋት ያለው ሲሆን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 1.38 በመቶውን የሚይዝ ነው፡፡ የሕዝብ ብዛት በተመለከተ በ1999 ዓ.ም. የብሔራዊ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መረጃ ፕሮጀክሽን መሠረት የክልሉ የሕዝብ አማካይ አመታዊ ዕድገት ምጣኔ 2.9 በመቶ ነው። የሕዝብ ዕድገት ምጣኔዉ በመኖሪያ አካባቢ በተመለከተ የገጠር ሕዝብ አመታዊ ዕድገት በ2.8 በመቶ ሲሆን በከተማ የሕዝብ የዕድገት ምጣኔ 4.8 በመቶ ነዉ ። በዚህ መሰረት በ2015 ዓ.ም. የክልሉ ሕዝብ 7,039,772 ይገመታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 80.7% በገጠር እና ቀሪዉ 19.3 % በከተሞች የሚኖር ነው፡፡ ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 6.47 በመቶውን የሚሸፍን ሲሆን የክልሉ አማካይ የህዝብ ጥግግት ደግሞ 464 ሰዎች በካሬ ኪ.ሜ ነው። ክልሉ በአሁኑ ወቅት በ7 ዞኖች/ ሀዲያ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ካምባታ፣ ሀላባ፣ የም ዞኖች/፣ በ3 ልዩ ወረዳዎች/ ጠምባሮ፣ ማረቆ ቀቤና ልዩ ወረዳዎች/ ፣ በ50 ወረዳዎች እና በ29 የከተማ አስተዳደሮች የተከፈለ ነው። ክልሉ 1294 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም 185 የከተማ 1109 የገጠር ቀበሌያት ናቸው፡፡ 

                                 የክልሉን ስነምህዳር በተመለከተ

 የማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የአየር ንብረቶች ይዟል በሚባል ደረጃ ለኑሮ ምቹ የሆኑ የደጋ፣ የወይና ደጋ እና የቆላ አከባቢዎች ያሉት ሲሆን በሁለት የተራራቁ 4 ጫፎች ያለው የአየር ንብረትም በክልሉ የተለያዩ ስነምህዳር (ecology) የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የተለያዩ የግብርና ሥርዓቶች፣ የአኗኗርና የባህል ብዝሀነት እንዲኖር አድርጓል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ ሥፍዎች እንደ ዘቢዳር፣ሙጎና አምባሪቾ ተራራዎች ሲሆኑ ዝቅተኛው ሥፍራ ደግሞ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በኦሞ ወንዝ አቅራቢያ ባለው የኦሞ ሸለቆ ጫፍ ከባህር ጠለል በላይ 447 ሜትር ከፍታ ያለው ሥፍራ ነው፡፡ 

 

 

 

Documents