Skip to main content

 

 

 

ሼክ አብራር ሽፋ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቃዲ

 

 

 

 

 

 

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 19/2016

 

“ቃዲ” ማለት በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ተሹሞ የሚሰራ ዳኛ ነው፡፡

 “ዋና ቃዲ” ማለት የክልሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ነው፡፡

   መቋቋም

ተጠሪነታቸው ለክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሆኑ

ሀ) የወረዳ የሸሪዓ ፍርድ ቤት

ለ) የዞን/የልዩ ወረዳ የሸሪዓ ፍርድ ቤት

ሐ) የክልል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ተቋቁሟል፡፡

መሰረታዊ ድንጋጌ

1- የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ከዚህ በታች በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ የወል የዳኝነት ስልጣን ይኖራቸዋል፡፡

ሀ) ማናቸውም የጋብቻ፣የፍች፣የቀለብ አወሳሰን፣አካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ሞግዚትነትና በቤተሰብ ተዛምዶ ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥያቄ ያስከተለው ጋብቻ በእስልምና ሐይማኖት ስርዓት መሰረት የተፈፀመ የሆነ እንደሆነ ወይም ባለጉዳዮቹ በእስልምና ሐይማኖት ስርዓት ለመዳኘት ፈቅደው ከሆነ፤

ለ) የወቅፍ፣የስጦታ/ሒባ፣የውርስ እንዲሁም የኑዛዜ ጉዳዮችን በተመለከተ አውራሽ ወይም ስጦታ አድራጊ ወይም ተናዛዥ ሙስሊም የሆነ እንደሆነ ወይም ሟች በሞተበት ሰዓት ሙስሊም ሆኖ የሞተ እንደሆነ ወይም ባለጉዳዮቹ በእስልምና ሐይማኖት ስርዓት ለመዳኘት ፈቅደው ከሆነ፤

ሐ) ከፍ ብሎ ከ(ሀ) እስከ (ለ) በተገለፁት ጉዳዮች ላይ ክሶች ኪሳራ መወሰንን በተመለከተ፤

2- ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የሁለት ፍርድ ቤቶች ስልጣን ያላቸው ተከራካሪዎች ጉዳያቸውን በእስልምና ሐይማኖት አማካይነት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለማሳየት ግልፅ በሆነ ሁኔታ በፍላጎታቸው መርጠው ከቀረቡ ብቻ ይሆናል፡፡

ፈቃደኝነትን ወይም ተቃውሞን ስለመወሰን 

1- ከተከራካሪ ወገኖች አንዱ በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት አቤቱታ ሲያቀርብ ጉዳዩ የቀረበለት የሸሪዓ ፍርድ ቤት ሌላው ተከራካሪ ወገን በፍርድ ቤቱ ለመዳኘት ፈቃደኛ ከሆነ ፈቃደኛ መሆኑንና የክሱን መልስ፣ፈቃደኛ ካልሆነ ደግሞ ተቃውሞውን ይዞ እንዲቀርብ የጥሪ ደብዳቤ ይላክለታል፡፡

2- በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 1 በተገለፀው መሰረት የፍርድ ቤቱ መጥሪያ በአግባቡ እንዲደርሰው የተደረገ ተከራካሪ ወገን ተቃውሞውን ወይም ፈቃደኝነቱን ለፍ/ቤቱ ሬጅስትራር ቀርቦ ካላረጋገጠ ተቃውሞ ለማቅረብ እንዳልፈለገ ተቆጥሮ ጉዳዩ በሌለበት ይታያል፡፡

3- በሸሪዓ ፍርድ ቤቶቹ ለመዳኘት በተከራካሪ ወገኖች መካከል ግልፅ በሆነ መንገድ ስምምነት በሌለ ጊዜ ጉዳዩ የቀረበለት የሸሪዓ ፍርድ ቤት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን በመደበኛው ፍርድ ቤት እንዲያስወስኑ ጉዳዩን ስልጣን ላለው የክልሉ መደበኛ ፍርድ ቤት ያስተላልፋል፡፡

4- በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 3 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው ያልተስማሙ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ለዳኝነት የተከፈለ ወጪ ካለ ገንዘቡ እንዲመለስ በማዘዝ መዝገቡን ዘግቶ ተከራካሪዎችን ያሰናብታል፡፡

5- በተከራካሪ ወገኖች ፈቃድ ላይ ተመስርተው በሸሪዓ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙ ጉዳዮችን በማናቸውም ምክንያት ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት፤ወይም በመደበኛው ፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙ ጉዳዮችን ወደ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ተዘዋውረው እንዲታዩ ማድረግ አይቻልም፡፡

የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሚሰሩባቸው ህጎች 

1- የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የስልጣን ክልላቸውን መሰረት አድርገው የቀረበላቸውን ጉዳዮች ሲመረምሩ የሸሪዓውን ህግ መሰረት አድርገው ይዳኛሉ፡፡

2- ፍርድ ቤቶቹ የያዟቸውን ጉዳዮች ስርዓት ባለው ሁኔታ ለመምራት እንዲያስችላቸው በሸሪዓው ህግ የተመለከቱት የሥነ-ስርዓት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በስራ ላይ ያሉት የፍትሐብሔር ሥነ-ስርዓት ህጎችን ተከትለው ይሰራሉ፡፡  

የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን

የክልል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

1- የዞን ወይም የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣኑ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች፤

2- የዞን ወይም የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሰሚነት ስልጣኑ በሰጠው በማናቸውም ውሳኔ የሚቀርቡ ጉዳዮች፤

3- በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 1 እና 2 የተመለከቱት አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፡-

ሀ) አንድ ጉዳይ ከአንድ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ወደ ሌላ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ተዛውሮ እንዲታይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

ለ) የሸሪዓ ህግን አስመልክቶ በክልሉ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ችሎቶች መካከል የህግ ትርጉምና ፍቺ የሚፈልጉ ጉዳዮችን የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

የዞን/የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን

1- የዞን/የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ግምታቸው ከብር 3,000,000 (ሦስት ሚሊየን) በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ይኖረዋል፡፡

2- የዞን/የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ በይግባኝ የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

3- አንድ ጉዳይ ከአንድ የወረዳ/ከተማ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ወደ ሌላ የወረዳ/ከተማ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ወይም ወደራሱ እንዲዛወር የሚቀርብን ጉዳይ ለማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

 

 

የወረዳ/ከተማ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን

የወረዳ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ግምታቸው እስከ 3,000,000 (ሦስት ሚሊየን ብር) የሚሆኑ ጉዳዮችን ወይም በገንዘብ ሊተመን በማይችሉ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡

የክልሉ ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የስራ ቋንቋ

1- የክልሉ ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የስራ ቋንቋ አማርኛ ይሆናል፡፡

2- አማርኛ ቋንቋ ለማይችል ባለጉዳይ ፍርድ ቤቱ አስተርጓሚ ይመድብለታል፡፡