በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል - የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት
(ሆሳዕና ህዳር 30/2017 ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም!!" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን ማጠቃለያ በዓል በቡታጅራ ከተማ ተከብሯል
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ ባስተላለፉት መልዕክት ጾታዊ ጥቃት በተሰሩ ስራዎች መሻሻል መኖሩን ገልፀው አሁንም መልኩን ቀይሮ ጥቃቱ በየአካባቢው እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
በሴቶችና ህፃናት ላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጨምሮ የሀይል ጥቃት እንዳይፈጸም አደረጃጀቶችን በማጠናከር በጋራ መሰራት ይገባል ብለዋል።
ሁሉም በባለቤትነት የሴቶችን ጥቃት አካል በማድረግ ከንግግር ባለፈ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም ጥቃት ለመከላከል አጋር መሆን ይገባዋል ብለዋል።
በየትኛውም አካባቢ የሚፈፀመውን የሴቶችና ህፃናት ጥቃት ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ስራው ተጠናክሮ መሠራት አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ የባህላዊ ዳኝነትን ወደ ህጋዊ ስርዓት በማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስር በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት የአካልና የህይወት መስዕዋትነት ከማስከፈል ባለፈ በቤተሰብና በሀገር ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የሴት ልጅ ጥቃት የሁሉም አጀንዳ መሆን አለበት ያሉት ወይዘሮ ዘቢባ ቢሮው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በሁሉም መዋቅር ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ አክመል አህመዲን እንደገለፁት በሴት ልጅ ላይ ጥቃት አለመፈፀም ከራስ የሚጀምር ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
የሴቶችና የህፃናት ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
ቢሮው ከፍትህና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ፎረም የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን በመድረኩ የተሳተፉ ወንዶች የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም በማለት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ የቡታጅራ ሆስፒታል የሴቶችና ህፃናት የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማስጀመር ለማዕከሉ ድጋፍ ተደርጓል።
046-55-62-112




